ስለ ኢትዮጵያ ዜና መከታተል ካቆምኩ ሰንበትበት ብያለሁ።

ከብርሃኑ ነጋም ሆነ ከኃይለማርያም ደሳለኝ ያነሰ ብሔራዊ ስሜት ኖሮኝ አይደለም። ከአብዲሳ አጋም ሆነ ከዘርዓይ ደረስ (የግሌ ታሪክ ጸሐፊ ቢኖረኝ) የሚሰለፍ ያገር ፍቅር አለኝ። እውነት እውነት እላችኋለሁ ፈንድቶ ሊወጣ ቀን የሚጠብቅ አንድ ሺህ ቴዎድሮስ፣ አራት መቶ ባካፋ፣ ሦስት መቶ ዲነግዴ በዉስጤ አለ።

ውሸት እና ጉራ፣ መቅሰፍት እና ድንፋታ ማጣፈጫቸው የሆነው እነኢቲቪ እና ኢሳት (ሁለቱም ምህፃረ ቃላቸው አማርኛ ያልሆነው ግን በማን ትዕዛዝ ነው?) እንዲሁም መሰሎቻቸው ልቤን ስለሚያንሸራትቱት ነው። (ልብ እንዴት ይንሸራተታል የምትሉ አያቴን ጠይቋት)።

እና እናንተም ተቀላቀሉኝ።

ምናልባት ምናልባት አድማጭ ተመልካች ሲያጡ ይስተካከሉ ይሆናል። እንደተለመደው “ይኼ ትውልድ ያገር ስሜት የለውም” ይሉን ይሆናል። የናንተ የት እንዳደረስን እዩት በሏቸው።

እና እንደዚህ አገራዊ እና አንገብጋቢ ወሬ ሳይኖረኝ ሲቀር ስለ ህይወት ጥቃቅን ነገሮች አሰላስላለሁ።

የዉስጤን አጋፋሪ እንዳሻው እቀሰቅሳለሁ።

ዛሬ ታዲያ አውቶቡስ ተሳፍሬ ስሔድ ጆሮዬ ላይ ሙዚቃ ሰክቼ፣ ዐይኔ በመስኮት የመንገዱን ጥግ እያማተረ በመሃል ትልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ አረፈ።

በላያቸው እንዲያው ለነገሩ ማስያዣ ጣል የተደረገባቸው ጥንድ ጡቶች እንደ’ናሳ’ ሮኬት ተቀስረዋል። ከታችኛው ጥግ በቀጭኑ “ሁለቱን ባንድ ዋጋ” የሚል ጽሁፍ አለ።

በርግጥ የጡት ማስያዣውንም ሆነ የጽሁፉን መኖር ያስተዋልኩት ዘግይቼ ነው። እና የሚሸጥ ጡት ነው የመሰለኝ። ምን አልባት ወንድ ስለሆንኩ ይሆናል። ምናልባት ጎረምሳ ወንድ ስለሆንኩ ይሆናል። ምናልባት ባለጌ ጎረምሳ ወንድ ስለሆንኩ ይሆናል።

ግን ሴቷስ ብትሆን ይሄን ማስታወቂያ አይታ ብትሸወድ ይገርማል? ጨዋ ሴትስ ብትሆን? ኧረ መነኩሴስ ብትሆን?

በርግጥ ማስታወቂያው የኢቲቪ ልማታዊ ዜና ብቻ በሚነገርባት፣ በግዕዝ በሚቀደስባት፣ እርቃን ጸያፍ በሆነባት አገሬ( በነገራችን ላይ አገር ነው ሀገር?) ቢሆን ምናልባት ያስማማናል።

ጡትና ዳሌ በሚገዛበት፣ ጸጉር በሚተከልበት ጡንቻ በሚገጠምበት አገር(ብዙ መዘርዘር ይቻላል-ጾታም እንደሚቀየር ሳንዘነጋ) ግን የጡትና የጡት ማስያዣ ማስታወቂያ ቢያምታታችሁ ይቅር ትባላላችሁ።

ምስኪን አባቶቻችን

አሁን የኔ አሟሟት አሟሟት ነው ወይ?

ጉች ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ሳላይ።

እንዳሉ ኖረው ሞቱ።

እኛ የተባረክን ልጆቻቸው ግን ያሻንን አይነት ቅርፅና መጠን ያለው ጡት መግዛት በምንችልበት ዘመን ተፈጥረን። “ይኼ ማስታወቂያ የጡት ነው የጡት ማስያዣ?” ብለን ለመጠየቅም በቃን።

ይህን ወሬ አዲስ አበባ ላለ ጓደኛዬ ባጫውተው “ተመስገን በል እስቲ፤ ጉች ጉች ያለውን ቀርቶ ዘንበል ዘንበል ያለውንም ካየሁ ይኼው ስድስት ያህል አምባገነኖች ከስልጣን ወርደዋል” አለኝ።

የሞራል ጥያቄ ለጊዜው ይቆየንና፤

ለመርፌ ማስታወቂያ ዕርቃን ምን ያረጋል? ማለቴ መልዕክቱን የሚስት አይሆንም? ጡት ማስያዣ መሸጥ የፈለገው ድርጅት ጡቱን አድንቀን ብቻ ከሔድን ምን ያተርፋል?

አስተያየት ይጻፉ