ያገሬ ተቃርኖ

አዎ ግብዝ ነኝ።

እኔ ከማንም አስበልጬ ብፈጽመውም ሌላ ሰው ሲያደርገው ግን ሁሌም ስህተት ነው።

ቤቲ በትልቁ መስኮተ ትዕይንት ስትሳረር ሳይ ኡ ኡ ብያለሁ። ያገሬን ባህል በማርከሷ አካኪ ዘራፍ ብያለሁ።

አገሬ …

ያ ጨዋ ህዝቧ እያንዳንዷን ሌሊት በትጋት የሚሳረርባት ቢሆንም፣ ስደት የማይቀንሰው ጦርነት ያማያጎድለው፥ ኤድስ ያማያሳሳው በሞትና ስደት መሃል ይኼው ሁሌም ሽቅብ የሚተኮሰው ቁጥራችን የቅንዝራምነታችን ህያው ማስረጃ ቢሆንም..እሷ እንዴት ብላ በቲቪ፥ ለዚያውም በባለቀለሙ፥ ሊያውም…

አስገድዶ መድፈር አያሳስበኝም፥ ጠለፋ ጉዳዬ አይደልም፥ ያለ እድሜ ጋብቻ ምኔም አይደለ ጨዋ ስማችን  በሷና መሰሎቿ ድርጊት መጉደፉ ያንገበግበኛል…

እና ራሷን ቆርጣችሁ በብር ሰሃን አቅርቡልኝ።

ማነው ደሞ ያ ከያኒ ነኝ ባዩ…ኮራ ብሎ ስላጨሰው ዕጽ ይዘበዝብ ነበር አሉ።

በወዲያ ደሞ ሰዶማውያኑ ነጻ ካልወጣን ይላሉ።

እኔ ደሞ ሞቼ ነው ቆሜ እላለሁ።

ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ።

እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።

በሚለው ቃሉ አማኝ ብሆንም፤ “አትፍረድ፥ ይፈረድብሃል”ን ግድግዳዬ ላይ ብለጥፍም፤ ለዲሞክራሲ መስፈን ለግለሰብ መብት መከበር ወዘተ ወዘተ ብታገልም ዕጸ ፋርስ እና “ሉጢ” ግን እንዴት ሲባል ባገሬ ይስፋፋል?

እያልኩ የዛሬ ሳምንት መጻፍ ጀመርኩና በመሃል አንድ ነገር ብልጭ አለብኝ።

በአንድ እጄ ጣቶች ቆጥሬ ለምጨርሳቸው ዓመታት ካገሬ ወጥቼ በመቆየት ብቻ ይህን ያህል ያገሬ ሰው ወግ አጥባቂነት ተዘንግቶኛል ለካ።

አንዳንዴ ይህ ህዝብ ምን እንደሚያስደስተው፥ ምን እንደሚያስቆጣው፥ ምን እንደሚያለያየው፥ ምን አንድ እንደሚያደርገው ከሰለሞን እንቆቅልሽ በላይ ይጠንብኛል።

ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የመጠጥ ዉሃ አታገኙም።

እሺ።

መብራት ለተቸገሩ ጎረቤቶቻችን ስለምንለግስ ለናንተ በፈረቃ ነው የሚደርሳችሁ።

ችግር የለም።

ጤፍና ስኳር፥ ዘይትና ነዳጅ ለተመረጡ ቅዱሳን ብቻ ነው የሚዳረሰው።

በጾም ጸሎት እንገፋዋለን።

ሥራ አጥነት በወጣቱ ዘንድ ገና ሃያ አምስት በመቶ ብቻ ነው። እናም የጫት አቅርቦትን ጨምረናል።

ሹክራን።

በምንም ምክኒያት ቢሆን ማማረር፥ ሰልፍ መውጣት፥ ትንፍሽ ማለት አይፈቀድላችሁም።

ኧረ ምናባታችን ቆርጦን፤ ጭራሽ አናልመውም።

‘ሰዶማዊነት’ ባገራችን ስላለበት ሁኔታ ለመወያየት……

ኧረ ጎራው፥ ኧረ ጎራው…ዘራፍ የሥላሤ ባሪያ፥ የጠቅል’ አሽከር…

እኔ ግን እንዲህ እላለሁ…

ሀብት ንብረቴ ተዘርፎ ሌላው ሲከብር እኔ እየተራብኩ፥ ወገኔ በእስር በስደት፥ በበረሃና ባህር ሞት ሲያልቅ ድምጼን ካላሰማሁ፤ “ሰዶማዊነት” እንዴት ሲታሰብ ብዬ ትንፍሽ አልልም።

ምክኒያቱም እስርና ሰደት ጭቆና ሲሆን፥ “ሰዶማዊነት” ምርጫ ነው።

ጋሽ አበራ እንዳለው “በገዛ ቂጡ እኔ ምን አገባኝ”።

Advertisements